Ethiopian Railways Corporation

ቋንቋ

(ኢምባኮ፡- ሐምሌ 13/2015ዓ.ም)
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሱ የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ልጆች (ህፃናት) ማቆያ ማዕከል ሐምሌ 13 /2015 ዓ.ም አስመረቀ፡፡
በተሻሻለው የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ሴት የመንግስት ሰራተኞች በመውለዳቸው ምክንያት በስራቸው ላይ ውጤታማ እንዳይሆኑ የሚፈጥርባቸውን እንቅፋት በማስወገድ ያለ ምንም ስጋት እና ሀሳብ በሙሉ ኃይላቸው፣ ጉልበታቸው፣ እውቀታቸው እና ጊዜያቸው ተጠቅመው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ይረዳ ዘንድ ሁሉም የፌደራል የመንግስት ተቋማት የህፃት ማቆያ ማዕከል ማቋቋም እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህፃናት ማቆያ ማዕከል በመክፈት አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በዛሬው እለት በተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ህሊና በላቸው (ኢ/ር) በይፋ ተመርቋል፡፡
ህሊና በላቸው (ኢ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ብቁ ዜጎች ለማፍራት የህፃናት ድጋፍ እና እንክብካቤ ልዩ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት ባወጣው አዋጅ መሠረት ይህ የህፃናት ማቆያ ማዕከል ገንብተን ለአገልግሎት በማብቃታችን ወላጆች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ እናትነት ከባድ በመሆኑ ይህ ማዕከል መከፈቱ ወላጆች ልጆቻቸው በማዕከሉ እንክብካቤ ስለሚደረግላቸው ሙሉ ሀሳባቸውና አቅማቸውን ስራ ላይ በማዋል ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል ይህ ደግሞ ለሰራተኛውም ሆነ ለተቋሙ ትልቅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ አለው ብለው ማዕሉ እዚህ አንዲደርስ አሻራቸውን ላኖሩ የተቋሙ ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፋዲል ኢብራሒም በበኩላቸው በከተማዋ ያለውን የትራንስፖር ችግር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ህጻናት ልጆቻቸውን ይዘው ለሚመጡ ወላጆች በተቻለ አቅም ተጨማሪ ተሸከርካሪዎችን በመመደብ እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይም ክፍተቶችን በማየት በትራንስፖርት ረገድ ለህፃናቱ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የስርዓተ-ፆታና ማህበራዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቡድን ባለሙያ ወ/ት ሙኒት በልሁ ኮርፖሬሽኑ የመንግስትን አቅጣጫ ተከትሎ የህፃናት ማቆያ ማዕከሉን ለመክፈት የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች በተመለከተ በኮርፖሬሽኑ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ህንፃ ለማዕከሉ በሚያመች ሁኔታ መሰራቱን እና ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ይህንን አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ የፌደራል የመንግስት ተቋማት ተሞክሮ በመውሰድ ሰራተኞች (ነርስ፣ሞግዚት እና የፅዳት ሠራተኞች) እንዲሁም መሠረታዊ ቁሳቁሶችን አልጋ፣ፍራሽ፣ትራስ፣መጫወቻ የፅዳት እቃዎች፣የመሳሰሉ በማሟላት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ የህፃናት ማቆያ ማዕከሉ እዚህ አንዲደርስ ከዲዛይን፤ አቅርቦትና ግዢ፤የሰው ሀይል እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ተሟልተው አገልግሎት እንዲሰጥ የኮርፖሬሽኑ ማህበረሰብ ላበረከተው ከፍተኛ ጥረት አመስግነው በቀጣይም ድጋፋ ተጠናሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የህፃናት ወላጆች በበኩላቸው የህፃናት ማቆያው በመከፈቱ ከብዙ ተፅእኖዎች እንዳቃለላቸው ተናግረዋል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው በተጨማሪ ልጆቻችን ከእኛ ጋር በመዋላቸውእንክብካቤ የሚያደርጉላቸው ብቁ ባለሙያዎች በመኖራቸው ያለስጋት ስራችንን እንድናከናውን ረድቶናል ብለዋል፡፡Leave a Reply