Ethiopian Railways Corporation

ቋንቋ

የመንግሥት የልማት ድርጅት ይዞታ አስተዳደር ለኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትና ለኮርፖሬሽኑ የማኔጅመንት አባላት በኮርፖሬት ገቨርናንስና ፋይናንስ ስርዓት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል አካሄደ፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ወቅት የመንግሥት የልማት ድርቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሀ/ሚካኤል እንደገለጹት የልማት ድርጅቶች ውጤታማና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደር እና የኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓት መዘርጋትና ሥራ ላይ መዋሉን መከታተል የአስተዳደሩ አንዱ አላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የአሠራር ሥርዓቶችን ተፈጻሚ ለማድረግ የልማት ድርጅቶች ግልጸኝነት፣ፍትሐዊነት እና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ስርዓት በመዘርጋት የሥራ አፈጻጸማቸውንና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎች በአስተዳደሩ በኩል የተዘጋጁ ሲሆን ለመመሪያዎቹ ተግባራዊነት የሚያግዝ የግንዛቤ ሥልጠና በተለያዩ ጊዜያት ለልማት ድርጅቶች ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው ስልጠናው የእርስ በእርስ ትውውቅና የልምድ ልውውጥ እድል በመፍጠር በቀጣይ ሥራዎችን በተሻለ ለመቆጣጠርና ለመምራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ መጠሪያሽ ሀ/ጊዮርጊስ የአስተዳደሩ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ፋይናንስ ስርዓት ሥራ አስፈጻሚ የኮርፖሬት ገቨርናንስ ኮድን በተመለከተ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምደባ እና የሙያ ስብጥር፣ የሥራ አመራር ቦርድ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተግባርና ኃላፊነት፣የውስጥ ኦዲት ሥርዓት የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ርዕሶች ላይ ትኩረት አድርገው ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ሠይፉ ዋሾ የአስተዳደሩ የትራንስፎርሜሽንና አቅም ግንባታ ስራ አስፈጻሚ የሂሳብ ስረዛ፣ የፋይናንስ አስተዳደር፣የዲስክሎዥር አፈጻጸም እና የተለያዩ በአስተዳደሩ የወጡ መመሪያዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ተሳታፊዎቹም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ባወጣቸው መመሪያዎች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠርና የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ መካሄዱ ለሥራቸው የሚያግዝ መሆኑንና በቀጣይም እንደዚህ አይነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች በአስተዳደሩ በኩል እንዲዘጋጅ የጠየቁ ሲሆን የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

በማጠቃለያውም ወቅት የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) አስተዳደሩ በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ለሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለሥራቸው መሻሻል የሚያግዙ በመሆኑ የሥራ አመራር ቦርዱ ተቋሙን ስትራተጂክ በሆነ ጉዳይ ላይ ይበልጥ የሚደግፍ እንዲሆን እንደነዚህ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ተገቢነታቸው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ሥልጠና ላይ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች የተገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 Leave a Reply