Ethiopian Railways Corporation

ቋንቋ

ታህሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢምባኮ )

የገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ፕራይቬታይዜሽን ጽ/ቤት እና የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ከታህሳስ 16-17/2016 ዓ.ም የመስክ ጉብኝት አደረጉ፡፡

የጉብኝቱ ዓላማ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ማሻሻያ ለማድረግ በእቅድ ከያዛቸው ዘርፎች አንዱ የባቡር ዘርፍ በመሆኑ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስፈልጉ የፖሊሲ፣አስተዳደራዊ እና አደረጃጀት ላይ የማሻሻያ ሀሳቦችን ለማቅረብ የባቡር መሠረተ ልማቱን በመጎብኘት እና ከተቋሙ አመራሮች ጋር መወያየት አስፈላጊ መሆኑን በገንዘብ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ሪፎርም እና ፕራይቬታይዜሽን ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ደመቀ አባተ ገልፀዋል፡፡

በፕራይቬታይዜሽንና ሪፎርም ስትራክቸር መሠረት ኮርፖሬሽኑ ያዘጋጀው የቀጣይ አምስት አመት ስትራተጂክ እቅዱ የሚያሰራ መሆኑ ስለታመነበት ይህን ከመደገፍ አንፃር ኮርፖሬሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ለመዳሰሰ፤ ድጋፍ የሚፈልጉ ስራዎችን ለመለየት እና ጥንካሬዎቹን ለማጎልበት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ግብአት ለመሰብሰብ ጉብኝቱ አስፈላጊ መሆኑን የጉብኝት ቡድን አባላት አስታውቀዋል፡፡

የስራ ኃላፊዎቹ የባቡር መሠረተ ልማት እና አገልግሎት አሰጣጡን ማለትም የለቡ ባቡር ጣቢያ፣ የባቡር ስምሪት (OCC) ማዕከል፤ እንዶዴ የባቡር መሠረተ ልማት ጥገና ማዕከል፣ እንዶዴ የባቡር የጥገና ማዕከል፤ሞጆ ባቡር ጣቢያ እና የጭነት ማራገፊያ ደረቅ ወደብ እንዲሁም የአዋሽ ነዳጅ ዴፖ አገናኝ የባቡር ፕሮጀክት የመስክ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን በኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች እና በባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የቡድኑ አባላት የባቡር መሠረተ ልማት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ቢሆንም በዛው ልክ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንዳሉት በተለይ በባቡር መሠረተ ልማት ንብረት ዝርፊያ እና የደህንነት ችግሮች ምክንያት በሚፈለገው ልክ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ከጉብኝቱ ለመገንዘብ መቻላቸውን ጠቅሰው ለዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት እና በመቀናጀት ዘርፉ ውጤታማ የሚሆንበት የአሰራር ስርዓት ለማቅረብ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ተቋሙ የተሰጠውን ተልእኮ ከማሳካት አንፃር የበኩሉን ጥረት በማድረግ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ለውጦች ላይ ጉልህ ሚና እያበረከተ ቢሆንም እያጋጠሙ ያሉት የፋይናስ፣የዝርፊያ እና የደህንነት ጉዳዮች ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

 

 

 

 

 



Leave a Reply