Ethiopian Railways Corporation

ቋንቋ

ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም
(ኢምባኮ)
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎች በመቄዶንያ የአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በመገኘት የ300 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉን አስመልክቶ የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራች የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ‹‹በማዕከሉ ተገኝቶ ህሙማንን መጎብኘት ከእርዳታው በላይ ትልቅ ተግባር መሆኑን ገልፀው ዛሬ በዚህ ቦታ ተገኝታችሁ በርካታ ህሙማንን በመጎብኘታችሁ “ታምሜ ጠይቃችሁኛል”? የሚለውን ታላቁን የመፅሀፍ ቅዱስ ቃል ስለፈፀማችሁ ታላቅ በረከት አግኝታችኋል›› በማለት በማዕከሉ ተገኝተው ድጋፍ ያደረጉትን የኮርፖሬሽኑን የስራ ኃላፊዎች አመስግነዋል፡፡

የክብር ዶክተር ቢኒያም በለጠ አያይዘውም ማዕከሉ በቀጣይ ለሚያስገነባው በአስራ አንድ ሺህ አምስት መቶ (11,500) ካሜ ላይ የሚያርፍ ግዙፍ ህንጻ ኮርፖሬሽኑ የኮንስትራክሽን ተቋም እንደመሆኑ መጠን በሙያም በማሽነሪ አቅርቦትም ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክትና አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በማዕከሉ የሚገኙትን አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን ጎብኘተዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ህሊና በላቸው (ኢ/ር) በበኩላቸው “መቄዶንያ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ ትልቅ ተቋም መሆኑን ገልጸው ኮርፖሬሽኑ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ አቅም በፈቀደ መጠን የተጠየቁ የግንባታ እቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ ድጋፍ የሚያደርግና ሌሎች ለማዕከሉ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ግብዓቶችን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የማዕከሉ ሠራተኞች እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ሰባት ሺህ አምስት መቶ የሚሆኑ አረጋዊያን፣የአዕምሮ ህሙማንና በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን የያዘ መሆኑንና አሁንም በየቦታው ድጋፍ የሚሹ በርካታ የህብረብሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ይህም በአንድ ማዕከል ብቻ የሚቀረፍ ባለመሆኑ መቄዶንያ የሁሉም ሰው ኃላፊነት በመሆኑ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በገንዘብ፣ በጉልበትም በሙያም ማዕከሉን በአካል ተገኝቶ በመጎብኘትም ድጋፍ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 



Leave a Reply