የዜና መግለጫ

በቢሾፍቱ ከተማ የባቡር አካዳሚ ግንባታ ፕሮጀክት ለመጀመር የማህበረሰብ አቀፍ ውይይት ተካሄደ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: በቢሾፍቱ ከተማ የባቡር አካዳሚ ግንባታ ፕሮጀክት ለመጀመር የማህበረሰብ አቀፍ ውይይት ተካሄደ
የተጫነበት ቀን:  11/28/2018 4:41:53 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በቢሾፍቱ ከተማ የባቡር አካዳሚ ለማስገንባት ህዳር 13 ቀን 2011ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ውይይት አካሄደ፡፡ የባቡር አካዳሚው ለመገንባት ሁለት ዓመት እንደሚወስድና ለዚሁ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የሚውል ከቻይና መንግስት 58,814,640 የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን የባቡር አካዳሚው ግንባታ ፕሮጀክት ሃላፊ የሆኑት ኢ/ር ኪሩቤል ጥላሁን ገልፀዋል፡፡ የባቡር አካዳሚውን የማማከርና የዲዛይን ስራውን CREEC(China Railway Engineering Corporation) እየሰራ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን ለመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ 62 ሄክታር መሬት በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የተፈቀደ ሲሆን 23 ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ህንፃዎችን የሚያካትት ይሆናልም ተብሏል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ልዩ ልዩ የስራ ክፍል ሃላፊዎች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በፕሮጀክት አተገባበርና የማህበረሰብ ተሳትፎ፣ ወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ አሰላል እና የፕሮጀክቱ እንደሃገር ከሚኖረው ጠቀሜታ ባሻገር የአካባቢው ማህበረሰብ ስለሚኖረው ተጠቃሚነት የውይይቱ ርዕሰ ጉዳዮች ሆነው ቀርበዋል፡፡ በውይይቱ ወቅትም ለባቡር ፕሮጀክቱ ተነሽ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደዚህ ዓይነት ለሃገርም ሆነ ለእነርሱ የሚጠቅም ፕሮጀክት እንደማይቃወሙና እንደሚደግፉ እንዲሁም ከሚፈጠሩ ስራ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጠርና 880,000 ሰዓት የሚጠይቅ የጉልበት ስራ በጊዜያዊነት እንደሚፈጠርና ግንባታው አልቆ ወደስራ ሲገባም ለ150 ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጠር በስልጠና መስኩም በዓመት 1000 ሰልጣኞች በመጀመሪያው ምዕራፍ እንደሚያሰለጥንና የአካዳሚውን የመቀበል አቅም በዓመት ወደ 3000 እንደሚያደርስም ተገልጿል፡፡