የዜና መግለጫ

ለኮርፖሬሽኑ አመራር እና ሰራተኞች የአመራር ስልጠና ተሰጠ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል:  ለኮርፖሬሽኑ አመራር እና ሰራተኞች የአመራር ስልጠና ተሰጠ
የተጫነበት ቀን:  11/28/2018 4:34:46 PM
የዜናው አካል:  ለኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አመራር እና ሰራተኞች የአመራርነት ፅንስ ሀሳብና አተገባበር ላይ የሚያተኮር ስልጠና ከህዳር 14-15/2011ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ተሰጠ፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክቡር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ባለሙያዎች በትምህርትና በስራ ራሳቸውን ለማሻሻል ልምምድ በማድረግ እንደዚህ አይነት ስልጠና በለውጥ ሂደት ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ስልጠናው ሁሉም ሰው በስራው ውጤታማ ለመሆን ጥረት እንዲያደርግ ካልሆነም ያልሆነበት ምክንያት በማጥናት ራስን በማሻሻል ለሀገራችን ድህነት ቅነሳና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ስኬት አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት የአመራር ባለሙያ ዶ/ር አሰግድ ወርቃለማው ባደረጉት ገለፃ ጠንካራ አመራርተነሳሽነትን የሚፈጥር የአመራር ክህሎት መኖር፣ስራን በፕሮጀክት መልክ አቅዶ መስራት፣ትክክለኛ አመለካከት መያዝ፣ሰዓት አጠቃቀም፣ተግባቦት እና እምነት ፈታኝ ሁኔታዎች በመቋቋም ተወዳዳሪነት ያለው የስኬት መንገድ እንዲኖር ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡ አመራር መሪዎች የተቋማቸውን ራዕይ ለማሳካት አርቆ ለማሰብና ከስር ያለውን እምቅ አቅም በመገንባት እርካታ የሚገኝበት መንገድ በመቀየስ እያንዳንዱ ሰው መሪ እንደሆነ ለማሰብ ይረዳል ብለዋል፡፡ አመራር ማለት አንድ ሰው የሚመራውን አካል ወደተፈለገው ራዕይ ማድረስ መሆኑን ዶ/ር አሰግድ ገልፀው አንድ ድርጅት ያለበትን ሁኔታ የሚለካው አመራሮች ባገኙት ውጤት መሆኑን ገልፀዋለ፡፡ ማኔጅመንት ያለውን የሠው ሀይል በጀት በሀላፊነት ወስዶ የሚያስተዳድር ሊደርሺፕ ግን በጀትና የሰው ሀይል ባይኖረው እንኳን ፈተናዎችን ተቋቁሞ ከተጠበቀው በላይ መስራት የሚችል ለውጥ ለማምጣት የሚነሳሳና ያለውን አቅም ተጠቅሞ ሌሎችን አስተባብሮ ግቡን እንደሚያሳካ ገልፀዋል፡፡ አመራር አንድን ነገር ሊያሳካ አልያም ሊገለው እንደሚችል የጠቀሱት ዶ/ር አሰግድ አንድ ድርጅት ጥሩ መሪ ካለው የተሻለ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለዋል፡፡ ዶ/ር አሰግድ ለውጥ መምጣት ያለበት ከላይ ቢሆንም ከታችም ሆኖ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቅሰው አብዛኛው ጊዜ ከታች ያሉ አካላት ወይም ግለሰቦች የለውጥ ሀይሎች ሆነው ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ እነዚህ የለውጥ አውራዎች ናቸው ብለዋል፡፡ ጠንካራ ሊደርሺፕ/አመራር ለባቡር መሠረተ ልማት ስኬታማነት ያለው አስተዋፅኦ በተመለከተም የባቡር መሠረተ ልማት በሀገር እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም አብራተዋል፡፡ ባቡር ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመገንባት ቁልፍ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ አመራር ቁልፍ የለውጥ መሳሪያ መሆኑን አምኖ ወደ ትግበራ በመግባት በእቅድ የያዛቸውን ፕሮጀክቶች ለማሳካትም ሆነ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ለውጡን የሚሸከሙ መሪዎች ሊኖሩና ብዙ መሪዎች ማፍራት ሲቻል እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ የስልጠና ተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች በማንሳት ውይይት ተደርጓል፡፡ ዶ/ር አሰግድ የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች የዚህ ስልጠና አስፈላጊነት በማመን በቂ ዝግጅት በማድረግ መከታተላቸውና የነበራቸው የነቃ ተሳትፎ ለመለወጥ ያላቸው ዝግጁነት ያሳያል በማለት ሀሳባቸውን የገለፁ ሲሆን ኮርፖሬሽኑም ለዶ/ር አሰግድ ጊዜያቸውን ሰውተው ያላቸውን እውቀትና ልምድ ለማካፈል ለደረጉት ትብብር የማስታወሻ ለዶ/ር አሰግድ ሥጦታ በኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተበርክቶላቸዋል፡፡