የዜና መግለጫ

ዋና ስራ አስፈፃሚው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልገሎት ጎበኙ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: ዋና ስራ አስፈፃሚው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልገሎት ጎበኙ
የተጫነበት ቀን:  11/27/2018 12:03:57 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ክቡር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ጉብኝት አድርጉ፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ የጉብኝታቸው መጀመሪያ ከባቡር አገልግሎት መነሻ አቅጫዎች አንዱ በሆነው ጦር ሀይሎች አደባባይ አድርገዋል፡፡ ቃሊቲ በሚገኘው የአገልግሎቱ ዋና ቢሮ ሲጎበኙም የትራንዚት አገልግሎቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ሙሉቀን አሰፋ ስለ ባቡር መስመሩ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡ በቻይናው የባቡር ምህንድስና ኮርፖሬሽን/CREC/የተዘረጋው ይህ የባቡር መስመሩ ከሰሜን ደቡብ እና ከምስራቅ ምዕራብ አጠቃለይ 34 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ሁለት አቅጣጫዎች እንዳሉት ኢ/ር ሙሉቀን ገልፀዋል፡፡ ከሶስት አመት በፊት 41 ባቡሮች ከቻይና በማስመጣት ከቻይናው ሸንዘን ሜትሮ ግሩፕ ጋር የአስተዳደር ውል በመግባት ከ2 ብር እስከ 6 ብር ታሪፍ በመወሰን ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4፡00 ሰዓት በአጠቃላይ በቀን ለ16 ሰዓታት በሚያደርገው ጉዞ በአማካይ 120ሺ ተሳፋሪዎችን እንደሚያመላልስ ኢ/ር ሙሉቀን አስታውቀዋል፡፡ የቻይናው ሸንዘን ሜትሮ ግሩፕ ለሶስት አመት የማስተዳደር ስራውን ወስዶ ከኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ኢ/ር ሙሉቀን ጠቅሰው የቴክኖሎጂ ሽግግሩን እውን ለማድረግ በተደረገው ጥረት መሠረት በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውን ባለሙያዎች ተረክበው እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሁለቱም የባቡር መስመሮች 39 የቲኬት መቁረጫ ቢሮዎችና የባቡር ጣቢያዎች እንዳሉ፤ከአዲስ አበባ ስታዲየም እስከ ልደታ ድረስ ሁለቱም አቅጣጫዎች 2.66 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጋራ መስመር እንዲሁም 5 የጋራ ጣቢያዎች እንዳሏቸው ኢ/ር መሉቀን ገልፀዋል፡፡ የባቡር መቆጣጠሪያ፤የጥገና፤የስምሪት መቆጣጠሪያ፣እንዲሁም የመለዋወጫና ንብረት ማከማቻ ማዕከላት ጉብኝ የተደረገላቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ የሀይል መቆራረጥ፣መለዋወጫ እቃዎች አለመኖር፣በአግባቡ ታሪፍ የማይከፍሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መኖር እንዲሁም የስልጣን ውክልና ግልፅ የሆነ መመሪያ አለመኖር በአገልገሎት አሰጣጡ ላይ እንደ ችግር የሚነሱ ነገሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ክቡር ዶ/ር ስንታየሁ ለተዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራምና ለተደረገላቸው ገለፃ ለኮርፖሬሽኑ አመራርና ባለሙያዎች አመስግነዋል፡፡ የአዲስ አበበ ቀላል ባቡር አገልግሎት ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ የሀይል መቆራረጥ፣የመለዋወጫ እቃዎች ፤የጥገና አቅም እንዲሁም ችግር ሲፈጠር መቋቋም የሚቻልበት አቅም መፍጠር በሚሉት ነጥቦች ላይ ቅድሚያ በመስጠት መስራት እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ስንታየሁ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ ለዚህም አመራሩ የ100 ቀን ዕቅድ በማውጣት ትግበራውን መጀመር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡