የዜና መግለጫ

የኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት ችግሮችን ለመፍታት እያረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑ ተገለፀ፡፡


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል:  የኮርፖሬሽኑ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር  የትራንስፖርት ችግሮችን ለመፍታት እያረገ  ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የተጫነበት ቀን:  11/9/2018 12:07:09 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል እና በራስ አቅም ለመስራት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለፁ፡፡ ሚኒስትሯ ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት ጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር ዋና ስራ አስኪያጅ ተወካይ ኢ/ር ሳምራዊት አቡበከር ስለ ባቡር መስመሩ አጠቃላይ መረጃ ገለፃ አድርገዋል፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የከተማዋን ነዋሪ የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል በሚል ዓላማ 85 በመቶ ከቻይና መንግስት በተገኘ ብድር በ475 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የባቡር መስመር ዝርጋታ መካሄዱን በዚህም አገልግሎት መስጠት ከጀመረም ሶስት ዓመታትን ማስቆጠሩን ጠቅሰው የባቡር መስመሩ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4፡00 ሰዓት በአማካይ በቀን 120ሺ ተሳፋሪዎችን እንደሚያመላልስ ኢ/ር ሳምራዊት ገልፀዋል፡፡ አገልግሎቱ ሲጀመር የአስተዳደር ስራው ለቻይናው ሸንዘን ሜትሮ መሰጠቱን ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት ግን የኮንትራት ጊዜው እንደተጠናቀቀና በነበረው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ወቅት በባቡር አሽከርካሪነት፣በባቡር ቁጥጥር ማዕከል፣በባቡር ጥገና እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የሰው ሀይል በማሰልጠን በከ90 በመቶ በላይ በራስ አቅም እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ኢ/ር ሄኖክ ቦጋለ በኮርፖሬሽኑ የባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ተወካይ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ ስለ ተቋሙ አጠቃላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሁለት አቅጣጫዎች ማለትም ከሰሜን- ደቡብ እና ከምስራቅ ምዕራብ የተዘረጋ 34 ኪ.ሜ ርዝመት እና 39 የባቡር ጣቢያዎች እንዳሉ ጠቅሰው የፍጥነት ዲዛይኑ በሰዓት 80 ኪ.ሜ መሆኑ የሚጓዘው ግን በሰዓት 40 ኪ.ሜ እንደሆነ የዚህም ምክንያት የእግረኛና የተሽከርካሪ ማቋረጫዎች ስላሉ አደጋ እንዳይከሰት በሚል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የሀይል መቆራረጥ፣የተሽከርካሪና የእግኞች ማቋረጫዎች ላይ ጥንቃቄ አለማድረግ፣የመለዋወጫ እጥረት እንዲሁም የቲኬት መጭበርበር በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ተግዳሮች መሆናቸውን ኢ/ር ሄኖክ ገልፀዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመሆን ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የእግረኞች ማቋረጫ መንገዶች ለመስራት ዝግጅት ላይ መሆኑን፣ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እየተፈለገ እንዳለ በጊዜያዊነት ግን ባቡሩ ከሚያልፍባቸው አከባቢዎች የኤክክትሪክ ሀይል በመውሰድ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንዳለ በተጨማሪም ጀነሬተር ለመግዛት እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ስለአገልግሎት አሰጣጡ እና ተግዳሮቶቹ ላይ ግንዛቤ የለውም በመገናኛ ብዙሀን መልእክት ለምን አይተላላፍም፣20 ባቡሮች ብቻ ናቸው የሚሰሩት ይባላል፣ባቡሮቹ በተሰራው የፍጥነት ዲዛይን መሠረት ለምን አይጓዙም፣የተጠቃሚዎች አስተያየት/እርካታ/ምን ያህል ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ግንዛቤ በመስጠት አደጋዎችን ለመቀነስ ከትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር ተቀናጅቶ ለመስራት ጥረት ይደረጋል፡፡ የእግረኛ ማቋረጫዎች ቅድሚያ በተመረጡ ስድስት ቦታዎች ለመስራት ጥናት ተጠናቋል፣የመለዋወጫ እቃዎችን ለመግዛት የዶላር እጥረት ስለነበር ነው በቅርቡ ከተፈታ የባቡሮች ቁጥር ይጨምራል ሲሉ ኢ/ር ሄኖክ ተናግረዋል፡፡ በኮርሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ በበኩላቸው የባቡር ትራንስፖርቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከህብረተሰቡ ጋር ለማስተዋወቅ ለሰባት ወራት በነፃ ሲያመላልስ እንደነበር ከዛም በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ ለማስጨበት ጥረት እንደተደረገ ነገር ግን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተጨማሪ ውይይቶች እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ተ/ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር የኋላሸት ጀመረ በተነሱ ሀሳቦች ላይ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ቀጣይ የማስፋፊያ ስራዎች ላይ በዋናነት የአዲስ አበባ አስተዳደር ስለሆነ የሚወስነው በጀት እና ፕላን ከተገኘ ኮርፖሬሽኑ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው፣የህብረተሰቡ እርካታ በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት አለመሰራቱ በቀጣይ ግን አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙሀን ግንዛቤ መስጠት ላይ አጠናክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ፣ሙሉ በሙሉ በራስ ሀይል ለመስራት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሽግግሩን እውን ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት አለብን ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ኮርፖሬሽኑ በሀገሪቱ ምንም የባቡር መሠረተ ልማት ባልነበረበት ወቅት ከምንም ተነስቶ እዚህ ደረጃ ላይ ማድረሱ ሊመሰገን እንደሚገባ ገልፀው በቀጣይም ከሌሎች ባለድሻ አካላት ጋር በመሆን ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መ/ቤታቸው የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግና የባቡር ትራንስፖርቱ ከተማዋን ነዋሪዎች ላይ እየታየ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት በመቅረፍ ረገድ ትልቁን ድርሻ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡