የዜና መግለጫ

በኮርፖሬሽኑ የISO 9001, 2015 የጥራት ስራ አመራር ስርዓት የውስጥ ኦዲት ስልጠና ተሰጠ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: በኮርፖሬሽኑ የISO 9001, 2015 የጥራት ስራ አመራር ስርዓት  የውስጥ ኦዲት ስልጠና ተሰጠ
የተጫነበት ቀን:  11/5/2018 4:42:39 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከየስራ ክፍሉ ለተውጣጡ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ከኢትዮጵያ የደረጃዎች ምዘና ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በባቡር አካዳሚ የስብሰባ አዳራሽ የISO 9001: 2015 የጥራት ስራ አመራር ስርዓት የውስጥ ኦዲት ስልጠና ሰጠ፡፡ የደረጃዎች ምዘና ኤጀንሲ የተለያዩ የማኔጅመንት ስርዓት ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ የገለፁት በደረጃዎች ምዘና ኤጀንሲ የስልጠና ድጋፍና ክትትል የስልጠና ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳፋ ሂካ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ኮርፖሬሽኑ የISO 9001: 2015 የአሰራር ስርዓት ሰርቲፋይ ለማድረግ እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ ማሟላት ካለበት መስፈርት አንዱ የሆነውን ISO 19011:2018 ሲስተሙን ኦዲት ማድረግ የሚያስችል የኦዲት ስልጠና ሲሆን ኦዲት ሲደረግ ምን መደረግ አለበት፣ የኦዲት መርሆዎች ምንድናቸው፣ ኦዲተር ምን ማሟላት አለበት የሚሉትን እና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን የኮርፖሬሽኑን አሰራር እንዴት መሻሻል አለበት የሚለውንም ያካተተ ስልጠና መሆኑን አሰልጣኙ ገልፀዋል፡፡ ስልጠናው መሰጠቱ በጋራ መስራትን እንዴት ማጎልበት እንደሚቻል፤ የኮርፖሬሽኑን የአሰራር ስርዓት እንዴት መቆጣጠር፣መለካትና መገምገም እንደሚቻል ማሳየት የሚችል የአሰራር ስርዓትን መፍጠር የሚያስችል እንዲሁም እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ISO 9001:2015 ሰርቲፋይ ለማድረግ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ስራው ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ መሆኑንና በአንዳንድ አስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት ፕሮጀክቱ ተቋርጦ መቆየቱንና በታቀደው መሰረት መከናወን አለመቻሉን ገልፀው ከመስከረም 28 /2011 ጀምሮ ISO 9001, 2015 ሰርቲፋይ ለማድረግ በአዲስ መልክ እየተሰራ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የጥራት ስራ አመራር ስርዓት ማሻሻያ ፕሮጀክት ጸ/ቤት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢ/ር ቢንያም አያሌው አስታውቀዋል፡፡ ISOን ሰርቲፋይ ለማድረግ የመጀመሪያው ሂደት ቅድመ ዝግጅት ሲሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተከናውነው አብዛኞቹ ወደ ትግበራ ገብተዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የስርዓቱ የውስጥ ኦዲት ማድረግ መሆኑን የገለጹት ኢ/ር ቢንያም የውስጥ ኦዲት ለማድረግ ስልጠናውን የወሰደ ባለሙያ በማስፈለጉ ስልጠናው መሰጠት ማስፈለጉን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ሰልጣኞቹም ከዋናው መስሪያ ቤትና ከቀላል ባቡር የተውጣጡና የመጀመሪያውን የISO 9001, 2015 ስርዓት ስልጠና ከወሰዱ 97 ሰልጣኞች መካከል 25 ሰልጣኞች ሲስተሙን ኦዲት እንዲያደርጉ ተመርጠው ስልጠናውን የወሰዱ ሲሆን ከሰልጣኞች የሚጠበቀው ISO 9001, 2015 በሚጠይቀው መስፈርት መሰረት ኮርፖሬሽኑ በትግበራው ላይ ያለውን ክፍተት በመለየት የለውጥ አንቀሳቃሽ ሆነው እንደሚተገብሩ ተገልጿል፡፡ ስልጠናው ሲጠናቀቅም በቀጣይ ሲስተሙ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ስልጠናውን ከወሰዱት ኦዲተሮች ጋር የ3 ቀን ወርክሾፕ የሚዘጋጅ መሆኑን የገለፁት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ቢንያም ሲስተሙ ከመስፈርቱ አንፃር በየክፍሉ ያለውን አሰራር ክፍተቱን የመለየት ስራ ከተሰራ በኋላ ያላሟሉ ክፍሎች እንዴት ማሟላት እንዳለባቸው የሚያሳይ ወርክ ሾፕ ከየ ስራ ክፍሎቹ ጋር እንደሚኖርም ገልፀዋል፡፡ ስልጠናው ኦዲት በሚደረግበት ወቅት ከመጀመሪያው ጀምሮ መከናወን ያለባቸው ተግባራት ማለትም የኦዲቲንግ መርሆዎች፣ኦዲት እንዴት ይታቀዳል፣ ኦዲት እንዴት ሪፖርት ይደረጋል የሚሉትን በዝርዝርና በጥልቀት የሚያሳይ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ነው፡፡ ሰልጣኞቹም ስልጠናው አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን ገልፀው ስልጠና አሰጣጡና አቀራረቡም የተሻለ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም አንድን ተቋም ወይም መሰሪያ ቤት ኦዲት ለማድረግ መከተል የሚገባውን ሂደት ለማወቅ አስችሎናል ብለዋል፡፡