የዜና መግለጫ

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የባቡር ጉባኤ ተካሄደ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የባቡር ጉባኤ ተካሄደ
የተጫነበት ቀን:  9/19/2018 12:01:46 PM
የዜናው አካል:  ኢ.ም.ባ.ኮ (መስከረም 09/2011ዓ.ም) የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ቻይና አፍሪካ አድቫይዘሪ እና አር ዲ ኤን ግሎባል ከተባለ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር በመሆን የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የባቡር ጉባኤ ከመስከረም 7-8 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሸራተን አዲስ ሆቴል አካሄደ፡፡ በጉባኤው ላይ ከ40 የሚበልጡ ከአሜሪካ፣ ላቲን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ኤሽያና አፍሪካ የመጡ የካበተ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ የመሰረተ ልማት አልሚዎች፣ የባቡር ኩባንያዎች፣ የባቡር ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ የአየር ንብርት ፋይናስ ተቋማትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተቋማት ታሳታፊ ሆነዋል፡፡ በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ዴይታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ ጉባኤው መንግስት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በልዩ የፕረይቬታይዜሽን ማእቅፍ ስር አጋር አድርጎ ለመስራት እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረው ለአለም አቀፉ ተቋማት የአብረን እንስራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርባሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ብርሃኑ በሻህ በበኩላቸው ጉባኤው አጋር የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የባቡር አልሚዎችን ለመለየት እንደሚያስችል ጠቁመው ኢትዮጵያ ለተያያዘቸው የልማት ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የባቡር ሴክተር ልማት ሚና የላቀ መሆኑንና መንግስትም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ዘርፈ ብዙ የባቡር መሰረተ ልማት፣ ተጓዳኝ የባቡር ልማት፣ የባቡር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አገልግሎት ውስጥ እንደሆነ ያነሱት ዶ/ር ብርሃኑ የባቡር መስመሩ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ስለሆነ ምንም አይነት የካርበን ጋዝ ልቀት የማያስከትልና ኢትዮጵያ ከተያያዘችው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መስመር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል፡፡ የጉባኤው ዋና ኃላማ ዓለም አቀፍ የባቡር መሰረተ ልማት አሊሚዎችና የፋይናንስ ተቋማት ወደፊት ኮርፖሪሽኑ መንግስት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት በPublic Private Partnership (PPP) ማዕቀፍ ስር ለሚያስገነባቸው የባቡር መስመሮች ዓለም አቀፍ ተቋማቱ ፍላጎት እንዲያሳዩ ማድረግ ሲሆን በዚህም መሰረት በርካታ ተቋማት በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን አሳይተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ኢ/ር የኃላእሸት ጀመረ ኮርፖሬሽኑ እስካሁን ያስገነባቸውንና ወደፊት የሚያስገነባቸውን ብሄራዊ የባቡር መስመሮች ምንነትንና የሚያስፈለጋቸውን የገንዘብ መጠን ከአጠቃላይ አገራዊ የኢንቨስትመን አመራጮችና የቱሪዝም አቅም ጋር በማዛመድ ገለጻ አድርገዋል፡፡ ሌሎች የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎችም በተጓዳኝ የባቡር ልማቶች ፕሮጀክት(TOD)፣በጭነት ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ አቅርቦት ትስስር ፕሮጀክት፣ በከተማ ብዙኃን የባቡር ትራንስፖርት ስርዓት እቅድ፣በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ትራንስፖርት ኦፕሬሽንና የወደፊት አቅጣጫ እንዲሁም በባቡር አካዳሚ ልማት ዙሪያ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በጉባኤው ላይ 7 የሚሆኑ የካበተ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ የባቡር መሰረተ ልማት አልሚዎችና የፋይናንስ ተቋማት የሰሩትን ስራዎችና ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን ፍላጎት ያሳዩ ዓለም አቀፍ የባቡር መሰረተ ልማት አልሚዎችና የፋይናስ ተቋማት ከኢትዮጵያ የምድር ባቡር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር አንድ በአንድ (Business to Business-B2B) ጥልቀት ያለው ውይይትና ምክክር አድርገዋል፡፡ ጉባኤው ወደፊት ኮርፖሬሽኑ በPPP ማዕቀፍ አብሮአቸው ሊሰራ የሚችልባቸውን የካበተ ልምድ ያላቸውን የባቡር መሰረተ ልማት አልሚዎችና የፋይናንስ ተቋማት ማንነትን መለየት እንዲችል ያስቻለው ሲሆን ወደፊት መንግስት ከአለሚዎቹ ጋር ለሚኖረው የፓሊሲ ውይይት በር ከፋች እንደሚሆንም ይታመናል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ኢትዮጵያን ከወደብ ባለቤትና ጎረቤት አገራት ጋር ለማገናኘት፣ የተለያዩ የልማት ኮሪደሮችን ለማስተሳሰር፣ የኢንዱስትሪ ቀጠናዎችና ፖርኮች ያሉባቸውን አካባቢዎች ለማገናኘት፣ህዝብን ህርስ በእርስ ለማስተሳሰተርና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የምስራቅ-ምህራብ እና ሰሜን-ደቡብ አፍሪካ የባቡር ትስስር አጀንዳ እውን የሚሆንበት ስትራቴጂ ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን 689 ኪ.ሜ የሚረዝም የባቡር መስመር ዘርግቶ ወደ አገልግሎት አስገብቷ፡፡ አሁን ላይ ኮርፖሬሽኑ የ606 ኪ.ሜ የባቡር መስመር ግንባታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የባቡር መሰረተ ልማት ቀጣይ መሆን ስላለበትና ያለውን የገንዘብ እጥረት በPPP ማዕቀፍ እና በራስ ኃይል የመገንባት አቅምን ለማዳበር ኮርፖሬሽኑ መጠነ ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡