የዜና መግለጫ

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ተኮር ልማት(TOD) ዙሪያ ውይይት አካሄደ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ተኮር ልማት(TOD) ዙሪያ ውይይት አካሄደ
የተጫነበት ቀን:  7/23/2018 4:30:23 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንዚት ተኮር ልማት(TOD) ፕሮጀክት ትግበራ ለመጀመር ከተቋቋሙ የአስተባባሪ ቴክኒካል ኮሚቴዎች ጋር በኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡ በውይይቱ ንግግር ያደረጉት በኮርፖሬሽኑ የንግድ ስራዎች ማበልፀጊያ መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሸዋንግዛው ክፍሌ የትራንዚት ተኮር ልማት ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በተመረጡ አራት የባቡር ጣቢያዎች በስምንት መቶ ሜትር ራዲየስ ክልል ውስጥ በሚገኙ ቦታዎች የሚገነቡ የተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት መሆኑንና የተመረጡ አራት የባቡር ጣቢያዎችም ለገሃር፣ቅድስት ልደታ፣አውቶብስ ተራና ዳግማዊ ምኒሊክ አደባባይ ባቡር ጣቢያዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በእነዚህ የተመረጡ ባቡር ጣቢያዎች በስምንት መቶ ራዲየስ ክልል ውስጥ ያሉ ባዶ ቦታዎች፣ ለመልሶ ማልማት የተመረጡ ቦታዎች፣ ለአልሚዎች የተሰጡ እና ባለቤትነት ያላቸው ቦታዎች ተለይተው ለአዋጭነት ጥናት ግብዓት እንዲሆኑ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ማኔጅመንት ቢሮ የአዲስ አበባ መሪ ማስተር ፕላን ማግኘት መቻሉንና ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር የቶፖግራፊና ካዳስተራል ማፕ ለማሰራት ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡ በኮርፖሬሽኑ የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ቴክኒካል ቡድን ከፍተኛ ሲቪል መሃንዲስ የሆኑት ኢ/ር ደሳለው ፍሥሃ ባቀረቡት ገለፃ የትራንዚት ተኮር ልማት(TOD) ያለው ጠቀሜታ፣ የኮሚቴው አወቃቀር፣ የኮሚቴው ተግባርና ሃላፊነት እንዲሁም ኮሚቴው ሊከተለው ስለሚገባ ዲስፕሊን አብራርተዋል፡፡ ኮሚቴዎቹ ለፕሮጀክቱ ከተመረጡ አራቱ ባቡር ጣቢያዎች ከሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች፣ ከወረዳዎች፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና ፕሮጀክቱን በአማካሪነት ከሚያከናውነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ኮርፖሬሽን የሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች የተውጣቱ ሰላሳ ሁለት(32) አባላት የተካተቱ ሲሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ የአካባቢውን አመራርና ህብረተሰብ በማስተባበር ሁኔታዎችን ምቹ ማድረግ የኮሚቴዎቹ ተግባርና ሃላፊነቶች መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡ የትራንዚት ተኮር ልማት(TOD) የከተማ ልማትን በማበረታታት፣ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን በማሳደግ፣አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ ፍትሃዊ የሃብት አጠቃቀም በማስፈን፣ ወጪን በመቀነስና የኢነቨስትመንት ወጪን በመተካት የላቀ ሚና ያለው መሆኑን ኢ/ር ደሳለው ገልፀዋል፡፡