የዜና መግለጫ

የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት 75 በመቶ መድረሱ ተገለፀ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት 75 በመቶ መድረሱ ተገለፀ
የተጫነበት ቀን:  6/29/2018 9:44:21 AM
የዜናው አካል:  ግንባታው በሁለት ምዕራፍ እየተከናወነ የሚገኘውና በአጠቃላይ 392ኪ.ሜ የሚሸፍነው የአዋሽ-ወልድያ/ሃራገበያ የባቡር ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈፃፀም 75 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢ/ር አብዱከሪም መሃመድ ገለፁ፡፡ ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ 270 ኪሜ የሚረዝመውና በአንደኛው ምዕራፍ የሚገኘው የፕሮጀክቱ የመጨረሻ የግንባታ ምዕራፍ ላይ ሲሆን አፈፃፀሙ 96 ከመቶ መድረሱንና ቀሪ 4 ፐርሰንቱ ከሃይል አቅርቦት ጋር የተያያዙ የማጠናቀቂያ ስራዎች መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪያጁ በቀጣይ አራት ወራት ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ወሳኝ የግንባታ ምዕራፎች የሚባሉት በርካታ ዋሻና ድልድዮች የሚገኙ ሲሆን አጠቃላይ በፕሮጀክቱ ካሉት አስራ ሁለት ዋሻዎች መካከል ሙሉ በሙሉ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ስድስት ዋሻዎች በምዕራፍ አንድ የሚገኙ ሲሆን ከዋሻዎች በተጨማሪም ሃምሳ አምስት ድልድዮች ይገኛሉ ያሉት ኢ/ር አብዱልከሪም ግንባታቸው የተጠናቀቁ አርባ ሁለቱ ድልድዮች በመጀመሪያው ምዕራፍ ሲገኙ ቀሪዎቹ በሁለተኛው ምዕራፍ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ከኮምቦልቻ እስከ ወልድያ/ሃራገበያ 122ኪ.ሜ የሚረዝመው የፕሮጀክቱ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ አፈፃፀሙ 35 ከመቶ የደረሰ ሲሆን በዚህ ምዕራፍ ከሚገኙ ስድስት ዋሻዎች ውስጥ አራቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ረዥሙና ሁለት ኪ.ሜ የሚሸፍነው ወልድያ አካባቢ የሚገኘውን ጨምሮ የሁለት ዋሻዎች አፈፃፀም ደግሞ 50 ፐርሰንት ላይ መድረሳቸውን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በኮርፖሬሽኑ ከተገነቡና እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች የተለየና የቅርብ ጊዜ በሆነ ቴክኖሎጅና በአውሮፓውያን ስታንዳርድ እየተገነባ ያለ ነው ያሉት ኢ/ር አብዱልከሪም ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ኦፕሬሽን ሲገባም በአውሮፓውያን ማኔጅመንት ሲስተም የሚመራና ከአንድ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ በመሆን በአንድ ኦፕሬተር እስከ 26 የሚደርሱ ባቡሮችን መቆጣጠር የሚስችል አሰራር እንደሚኖረውም ገልፀዋል፡፡ ስልሳ ስድስት ወራት ጊዜ የተመደበለት ፕሮጀክቱ በታቀደለት የጊዜ ገደብና በተመደበለት በጀት መሰረት እየተከናወነ መሆኑና እ.ኤ.አ እስከ 2020 ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አስር የባቡር ጣቢያዎች የሚኖሩት ሲሆን አዋሽ፣ አሚባራ፣ ሸዋሮቢት፣ ሰምበቴ፣ ካራቆሬ፣ መኮይና ኮምቦልቻ በምዕራፍ አንድ እንዲሁም ሐይቅ፣ መርሳና ሃራ ገበያ ደግሞ በሁለተኛው ምዕራፍ የሚገኙ የባቡር ጣቢያዎች ናቸው፡፡