የዜና መግለጫ

የወልድያ/ሃራገበያ-መቀሌ የባቡር ፕሮጀክት 51 በመቶ መድረሱ ተገለፀ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: የወልድያ/ሃራገበያ-መቀሌ የባቡር ፕሮጀክት 51 በመቶ መድረሱ ተገለፀ
የተጫነበት ቀን:  6/8/2018 3:16:34 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እያስገነባቸው ከሚገኙ የባቡር ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የወልድያ/ሃራገበያ-መቀሌ ባቡር ፕሮጀክት እስከ ሚያዚያ 2010ዓ.ም ድረስ አጠቃላይ አፈፃፀሙ 51.5 ከመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ገብረመድህን ገብረአሊፍ ገለፁ፡፡ ከወልድያ/ሃራገበያ አንስቶ እስከ መቀሌ 216 ኪ.ሜ የሚሸፍነውና CCCC በተባለው የቻይና ተቋራጭ የሚገነባው ፕሮጀክቱ በአላማጣ፣መኾኒ፣አዲጉዶምና መቀሌ አራት የባቡር ጣቢያዎች የሚኖሩት ሲሆን ዘጠኝ ዋሻዎች፣ ሰባስድስት ትልልቅ ድልድዮች፣ ሶስት መቶ ሰባስድስት የውሃ ማፋሰሻዎችና የሰውና የእንስሳት መተላለፊያዎች እንዳሉት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ገልፀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ወሳኝ ምዕራፍ የሚባለው የዋሻዎች ግንባታ ሲሆን አፈፃፀሙም 97 በመቶ ደርሷል ያሉት ስራ አስኪያጁ የድልድዮቹ 56 በመቶ እንዲሁም የአፈር ቆረጣው ደግሞ 70 በመቶ መድረሱን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ አጠቃላይ ርዝመታቸው 10.33 ኪ.ሜ የሚሸፍኑት ዘጠን ዋሻዎች መካከል ወደ አፋር ክልል አካባቢ የሚገኙት ኮከሌ አንድ እና ሁለት፣ ማይጨልፎ፣ዳዳህ እና አከሰባ በሚባሉ አካባቢዎች ያሉት ሲሆኑ ትልቁና 3.66 ኪ.ሜ የሚሸፍነው ማይጨልፎ ዋሻ ግንባታው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገልጧል፡፡ የፕሮጀክቱ ወሳኝ ምዕራፎች በሚባሉት የዋሻና ድልድዮች ግንባታ ወቅት እስከ 5000 ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ነበር ያሉት ስራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅት የእነዚህ ግንባታዎች ከ95 በመቶ በላይ የተጠናቀቀ በመሆኑ የሰራተኞች ቁጥር መቀነሱን ገልፀው አሁን ባለው ሁኔታ ከ1200 በላይ ሰራተኞች አሉት ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ የስራ እድል ተጠቃሚ የሆኑና በአከሰባ ዋሻ በግንባታ ስራ ተሰማርተው ካገኘናቸው ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው በብየዳ ሙያ ላይ የሚሰራው አወት ሃይሉ ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ወጣቶች ጥሩ የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ለከተማዋና ለሃገር እድገት ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር በጉጉት እንደሚጠብቁት ወጣት አወት ገልፆልናል፡፡