የዜና መግለጫ

ኮርፖሬሽኑ የደህንነት መሳሪያዎች ግዢ ውል ተፈራረመ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: ኮርፖሬሽኑ የደህንነት መሳሪያዎች ግዢ ውል ተፈራረመ
የተጫነበት ቀን:  5/16/2018 2:51:46 PM
የዜናው አካል:  ኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ የደህንነት መሳሪያዎች ግዢ ስምምነት ውል ግንቦት 06/2010 ዓ.ም ከአቅራቢ ተቋማት ጋር ውል መፈጸሙን አስታወቀ፡፡ የኢምባኮ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብርሀኑ በሻህ፤የስሚዝ ዲተክሽን የፋይናስ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ማርክ ኒክ ኤርሚኒክስ እና የራፒ ስካን ሲስተምስ ሊሚትድ አፍሪካ ካርጎና ስካኒንግ ሶልሽን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ፖል ሆሊንግ ሸድ በደህንነት መሳሪያዎች ግዢ በውል ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡ የኢ.ም.ባ.ኮ. ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ብርሀኑ በሻህ የደህንነት መሳሪያዎቹ ግዢ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን አስተማማኝ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በውሉ መሠረት መሳሪያዎቹ ተገጥመው ለታሰበው ዓላማ እንደሚውሉ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ በኮርፖሬሽኑ የምህንድስና ግዢ መምሪያ ኃላፊ ኢ/ር በሀይሉ ስንታየሁ የደህንነት መሳሪያዎቹ ግዢ የተከናነው በዓለም ዓቀፍ ውስን ጨረታ መሆኑን ጠቅሰው አሸናፊዎቹም የፈረንሳይ ስሚዝ ዲቴክሽን እና የአሜሪካው ራፒ ስካን የተባሉ ኩባንያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ አቅራቢዎቹ በገለልተኛ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰነዳቸው ተገምግሞ ብቁ ሆነው በመገኘታቸው እንደተመረጡ ኢ/ር በሀይሉ ገልፀዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች የደህንነት መሳሪያዎቹን አምርተው ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት ገጥመው ሙከራ በማድረግ መስራታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ርክክብ እንደሚደረግ ኢ/ር በሀይሉ ገልፀዋል፡፡ የደህንነት መሳሪዎቹ የትግበራና ቁጥጥር ስራ በዋናነት በመረጃና ደህንነት ባለሙያዎች እንደሚከናወን ኢ/ር በሀይሉ ጠቅሰው ቴክኖሎጂው ለሀገሪቱ ለአዲስ በመሆኑ ለሌሎች ባለድርሻ አካላትም በአጠቃቀሙ ላይ ስልጠና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ የእነዚህ መሳሪያዎች መገጠም መንግስት የመሠረተ ልማቱን አስፈላጊነት አምኖ በብዙ ወጪ ያስገነባው በመሆኑ የመሠረተ ልማቱን እና የደንበኞችን ደህንነት አስተማማኝ እንዲሆን ያደርገዋል ያሉት ኢ/ር በሀይሉ በተጨማሪም ደህንነት የዓለም ዓቀፍ የባቡር ፕሮጀክቶች መስፈርት አንዱ በመሆኑ ህጉን በማክበር ተወዳዳሪ እና ውጤታማ ለመሆን መሳሪያዎቹ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡ ኢ/ር በሀይሉ ይህ የግዢ ሂደት በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ላደረጉ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ፤የኦዲት አገልግሎት፤የህግ አገልግሎት ፤ የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል፤ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡