የዜና መግለጫ

በኮርፖሬሽኑ የ2010 በጀት የ9ወር እቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሄደ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: በኮርፖሬሽኑ የ2010 በጀት የ9ወር እቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሄደ
የተጫነበት ቀን:  4/2/2018 3:15:23 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አመራር አካላትና ሰራተኞች በኮርፖሬሽኑ የ2010 በጀት ዓመት የ9ወር እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሄዱ፡፡ ዋና ስራ አስፈፃሚውን ወክለው የውይይት መድረኩን የከፈቱት የኮርፖሬሽኑ የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር የኋላእሸት በንግግራቸው በበጀት አመቱ የመጨረሻ ሩብ አመት ስራዎች፣ የኮርፖሬሽኑ የወደፊት አቅጣጫና ሰራተኛው ከማኔጅመንቱ እንዲሁም ሰራተኛው ዕርስ በርሱ ያለው ውስጣዊ ግንኙነትን ለማጠናከር በየ3 ወር ከሚደረገው መደበኛ መድረክ በተጨማሪ ሌሎች ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ በውይይት መድረኩ በዋናነት የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም ክረምት ላይ በነበረው የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ከሰራተኞች የቀረቡ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ከመንግስት የልማት ድርጅቶች አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ አጣሪ ኮሚቴው የደረሰበት ውጤት በመድረኩ ቀርቧል፡፡ የበጀት ዓመቱን የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑ ፕላኒንግ መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ሜላት ፀጋዬ በዘጠኝ ወራት በባቡር መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ጥሩ አፈፃፀም የታየበት መሆኑን ገልፀው የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ወደ አገልግሎት ለማስገባት እንዲሁም በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የርክክብ ስራ የሲስተም ፍተሻ መካሄዱን ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሁለቱም መስመሮች 48.6 ሚሊየን መንገደኞች በማጓጓዝ 145.8 ሚሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 29 ሚሊየን መንገደኞች በማጓጓዝ 87.7 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱንና ከትራንስፖርት ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ ያለበትን ብድር መክፈል የሚያስችል ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያስችሉ ስራዎች ለመስራት እንደታቀደ ሃላፊዋ በሪፖርቱ ገልፀዋል፡፡ በጥልቅ ተሃድሶ መድረክ ወቅት ከሰራተኞች የተነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎችን የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ የደረሰበትን ውጤት ያቀረቡት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የሚያጋጥመውን የሃይል መቆራረጥ በዘላቂነት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በመድረኩ በአጣሪ ኮሚቴው በልዩ ሁኔታ የታዩና ክትትል የተደረገባቸው ጉዳዮች በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ የባቡር ሴክተር ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ የተመለከተ ሰፋ ያለ ስትራቴጂክ እቅድም በባቡር አካዳሚ ተጠባባቂ ም/ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዓብይ ጌታቸው ቀርቧል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች መድረኩ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ገልፀው የቀረቡ አጀንዳዎች ካላቸው ወሳኝነትና ስፋት አንፃር ለመድረኩ የተያዘው ጊዜ በቂ አለመሆኑ ሰፋ ያለ ጊዜ ቢሰጥ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል፡፡