የዜና መግለጫ

ኮርፖሬሽኑ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለማከናወን ጥናት እያደረገ መሆኑን ገለፀ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: ኮርፖሬሽኑ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለማከናወን ጥናት እያደረገ መሆኑን ገለፀ
የተጫነበት ቀን:  3/29/2018 3:20:44 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በሀገሪቱ ለተገነቡ የባቡር መሠረተ ልማቶች የተገኘውን ብድር ለመመለስና በቀጣይ ለሚገነቡ የባቡር ፕሮጀክቶች በራስ አቅም ለመገንባት እንዲያስችል ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ የንግድ ስራዎች ለመስራት ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በኮርፖሬሽኑ የንግድ ስራዎች ማበልፀጊያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽዋንግዛው ክፍሌ እንዳሉት የመምሪያው ዋና ተልዕኮ ለኮርፖሬሽኑ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን በማጥናት ወደ ተግባር መለወጥ መሆኑን እና ይህም ኮርፖሬሽኑ ግንባታቸውን አጠናቀው አገልግሎት የጀመሩ የባቡር መስመሮችም ሆኑ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የባቡር ፕሮጀክቶች 80 በመቶ በብድር የተሰሩ በመሆናቸው የብድር ጫናውን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ በቀጣይ የሚዘረጉ የባቡር መስመሮች በራስ አቅም ለመስራት እንዲያስችል ተጨማሪ የገቢ ምንጮችን በማጥናት የንግድ ስራዎችን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት አቶ ሽዋንግዛው ይህንን ለማከናወን ከቻይና፣ደቡብ አፍሪካ፣እንዲሁም ከአውስትራሊያ ልምድ በመውሰድና በማጥናት የተለያዩ የንግድ አማራጮችን ይዞ ለመስራት እንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ሽዋንግዛው ባቡር በኤሌክትሪክ የሚሰራ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀም በመሆኑ ለአየር ንብረት መዛባት አሉታዊ ተፅእኖ ስለሌለው ይህንኑ በሚመለከት ጥናት በማድረግ ለአለም ዓቀፍ የፋይናስ ተቋማት በመሸጥ ገቢ ማግኘት እንዲቻል ቻይና አፍሪካ አድቫይዘር ግሩፕ ከተባለ ተቋም ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሚያቋርጥባቸው አከባቢዎች ማለትም ለገሀር፣ልደታ፣አብቶቡስ ተራ እና አራዳ ጊዮርጊስ ቦታዎች ተመርጠው ለንግድ ስራ የሚሆኑ የተለያዩ ህንፃዎች ለመገንባት ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራሞ የቅድመ አዋጭነት ጥናት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን አቶ ሽዋንግዛው ጠቅሰዋል፡፡ በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ የፍላጎት ጥናት/Expression of Interest/ ተዘጋጅቶ አብሮ ለመስራት የሚፈልጉ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት እቅድ እንዳለ የጠቀሱት አቶ ሽዋንግዛው የሎጂስትቲክስ፣የባቡር ቱሪዝም፣ማስታወቂያ እንዲሁም ሌሎች የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች በመስራት የተቋሙን ራዕይ ለማሳካት ዕቅድ ተይዞ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ፋይናንስ ከማፈላለግ ባሻገር ሁሉንም የባቡር ፕሮጀክቶች ወጪና የባቡር ትራንስፖርት ወጪ ከመንግስት ከሚመደብ በጀትና ከውጭ አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ብቻ መወሰን አዋጭ አለመሆኑ ያነሱት አቶ ሽዋንግዛው የዚህ አይነት አማራጭ የገቢ ምንጭ በማፈላለግ የበጀት ክፍተትን መሙላት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በእቅድ ያሉት የንግድ ስራዎች ለኮርፖሬሽኑ የብድር ጫናን ከማቃለል ባለፈ የስራ እድል ፈጠራ እና ለከተማ ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ሲሉም አቶ ሽዋንግዛው ተናግረዋል፡፡