የዜና መግለጫ

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር አማራጭ እንዲኖር ማድረጉ ተነገረ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር አማራጭ እንዲኖር ማድረጉ ተነገረ
የተጫነበት ቀን:  3/23/2018 9:39:33 AM
የዜናው አካል:  የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ከታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከጅቡቲ-ሞጆ ደረቅ ወደብ የጭነትና እስከ ለቡ /አዲስ አበባ/ ድረስ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ በርካቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስታወቀ፡፡ በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና የኦፕሬሽን ኃላፊ አቶ ተሾመ እሸቴ የባቡር ትራንስፖርቱ በይፋ ስራ ከተጀመረ ከሁለት ወር በላይ ማስቆጠሩን ገልፀው የጭነት አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት የመንግስት /መልቲ ሞዳል/ትራንስፖርት በየቀኑ 53 ኮንቴነር ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ እንደሚጫን ገልፀው የግል /ዩኒ ሞዳል/ ጭነት እስካሁን አለመጀመሩ ለዚህም ምክንያቱ በእንዶዴ የባቡር ጣቢያ አገናኝ መንገድ ባለመሰራቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የህዝብ ትራንስፖርትን በተመለከተ በየሁለት ቀኑ /እ.ኤ.አ በሙሉ ቁጥር/የቀን ቁጥሮች/ ከፉሪ/ለቡ/ባቡር ጣቢያ መነሻነት ወደ ጅቡቲ የሚጓዝ መሆኑን በዚህም በአማካኝ ከ350-400 ሰው እንደሚሳፈር ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም የጭነት በቀን ሁለት ጊዜ የህዝብ ደግሞ በየቀኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ዕቅድ እንዳለ አቶ ተሾመ ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ በዋናነት የሀገሪቱን ወጪ ገቢ ንግድ ለማቀላጠፍ ባለው አቅም አገልግሎት ለመስጠት ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን ባቡሩ የሚያቋርጥባቸው አከባቢዎች ያሉ የህብተሰብ ክፍሎች የመንገድ አጠቃቀም ችግር፣ በየጣቢያዎች አገናኝ መንገድ አለመሰራት፣ውሃ፣መብራት አለመኖር፣በጀት በወቅቱ አለመለቀቅ እንዲሁም አስፈላጊ የሰው ሀይል ቅጥር አለመደረጉ እንቅፋት እንደፈጠረበት አቶ ተሾመ ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮንትራት አስተዳደርና ፕሮጀክት ትግበራ መምሪያ ኃላፊ ኢ/ር እስክንድር መሐመድ በበኩላቸው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር የሀገሪቱን ወጪ ገቢ የንግድ እንቅስቃሴ ያሳልጣል በሚል ራዕይ የተገነባ መሆኑን ጠቅሰው የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጥም ቀሪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በባቡር መስመሩ ባሉ ጣቢያዎች የውሃና መብራት መስመር ዝርጋታዎች እንዲሁም የአብዛኛዎቹ አገናኝ መንገዶች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው የለቡ፣እንዶዴና ቢሾፍቱ ጣቢያዎች ግን የወሰን ማስከበር ስራዎች ባለመጠናቀቃቸው ዘግይተዋል ብለዋል፡፡ አሁን ግን የካሳ ክፍያ በመከናወኑ የግንባታ ስራው መጀመሩና እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል፡፡ የፍተሻ መሳሪያዎች እና መጠባበቂያ ጀነሬተር ግዢን በተመለከተም የጨረታ ሂደቱ ተጠናቆ አሸናፊው ድርጅት እቃዎቹን እስሚያቀርብ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ መነሻውን ለቡ ፉሪ ባቡር ጣቢያ አድርጎ በአዳማና ድሬዳዋ የባቡር ጣቢያዎች በማለፍ መዳረሻው ጅቡቲ ነጋድ የሆነው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት በምቾት፣ፍጥነት እንዲሁም በደህንነቱ ለህብረተሰቡ ያመጣው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን እና አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ማስቻሉን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል፡፡ አቶ ቅጤሳ ጌሱ እና ተማሪ በረከት ጌትነት የተባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ባቡሩ ለተጓዦች ምቹ መሆኑን ከጠቀሱት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ፣አዳማ፣ድሬዳዋ ያሉት የባቡር ጣቢያዎች ከከተማ ራቅ በማለታቸው የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት መኖርና ውድ መሆኑ፣የባቡር ጉዞው ፍጥነት አነስተኛ መሆን ፣በባቡር ጣቢዎችና በባቡር ውስጥ ምግብ አለመኖር እና ያለው አገልግሎትም ውድ መሆኑን፣ እንደ ችግር አንስተው በቀጣይ እነዚህ ነገሮች ከተሻሻሉ የባቡር አገልግሎቱ ይበልጥ ተመራጭ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡