የዜና መግለጫ

የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞችና የስራ ሃላፊዎች የሴቶች ቀንን አከበሩ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞችና የስራ ሃላፊዎች የሴቶች ቀንን አከበሩ
የተጫነበት ቀን:  3/15/2018 4:37:46 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሰራተኞችና የስራ ሃላፊዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ለ107ኛ እና በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ42ኛ ጊዜ “በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በኮርፖሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ አከበሩ፡፡ በፕሮግራሙ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙሉአለም ጌታሁን በኮርፖሬሽኑ ደረጃ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎች እየተካተቱ መሆኑን አንስተው ለዚህም በኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የስራ ክፍሎች የሚገኙ ሴቶች ጠንካራ የስራ እንቅስቃሴ ማድረግና ወደተሻለ የሃላፊነት ቦታ ላይ መምጣት አለባቸው ብለዋል፡፡ በስርዓተ ፆታና አካል ጉዳተኝነት ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ የግንዛቤ መፍጠሪያ ንግግር ያደረጉት የፕሮግራሙ ተጋባዥ እንግዳ በፊት የአካል ጉዳተኞች ማህበር ስራ አስኪያጅ የነበሩትና አሁን በኦስትሪያ ኢምባሲ የብሪጅንግ ጋፕ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ሽታዬ አስታውስ የኮርፖሬሽኑ የባቡር ትራንስፖርት አሰጣጥ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞችን ተደራሽ ያደረገ መሆኑን የተመለከተ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን በቦታው ከነበሩ ሃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በተለይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የግንባታ ዲዛይንና ሂደት ላይ ለተነሳው አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ጥያቄ በኮርፖሬሽኑ የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ም/ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢ/ር የኋላእሸት ጀመረ ምላሽ ሲሰጡ የባቡር መስመሩ አካል ጉዳተኞች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሊፍት አገልግሎት እና በባቡር ውስጥም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ማየት ለተሳናቸው የድምፅ እና መስማት ለተሳነናቸው የስክሪን መልዕክት እንዲያገኙ መደረጉን አንስተዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደረጀ ተፈራ እኛ ድጋፍ እያደረግንላቸው ያሉ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል ልናደርግላቸው ይገባል፡፡ ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ህፃናትንም በምንችለው ነገር ሁሉ በመደገፍ ለቁም ነገር ልናበቃቸው ይገባል እየተደጋገፉ መሄድ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ነው ብለዋል በፕሮግራሙ የመዝጊያ ንግግራቸው፡፡