የዜና መግለጫ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች በአሳንሰር /ሊፍት/ አገልግሎት ተደሰቱ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ተገልጋዮች በአሳንሰር /ሊፍት/ አገልግሎት ተደሰቱ
የተጫነበት ቀን:  3/15/2018 4:02:07 PM
የዜናው አካል:  የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት በከተማዋ ያለውን የህዝብ ጥያቄ ለመቅረፍ ሙሉ በሙሉ የአሳንሰር አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ደስታቸውን ገለጹ ፡፡ የባቡር አገልግሎቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ብዙ ተሳፋሪዎችን በማጓጓዝ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን ከጅምሩ የባቡር መስመሩ ሲገነባ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ/አመቺ/ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ሊፍት፣ስካሌተር፣ የድምፅ፣ የፅሁፍ መረጃዎችን የሚሰጡ እንዲሁም አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የባቡር አገልግሎት አመቺ እንዲሆን ከሚያደርጉት አንዱ የሊፍት መኖር ሲሆን ከታህሳስ 2010 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የአዲስ አበበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወቀ ሙሉ ገልፀዋል፡፡ አገልግሎቱን ለማስጀመር የዘገየበት ምክንያትም የሊፍት አጠቃቀም ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑና ብዙ ተገልጋዮችን የሚያስተናግድ ከመሆኑ አኳያ ኮንትራት አስተዳደሩ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያድርግ መቆየቱን አቶ አወቀ ገልፀዋል፡፡ በሁለቱም አቅጣጫዎች ማለትም ከሰሜን-ደቡብ እና ከምስራቅ-ምዕራብ 22 ሊፍቶች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁሉም አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አቶ አወቀ ነግረውናል፡፡ በአሳንሰሮቹ ወስጥ በዘርፉ የሰለጠኑ 57 ባለሙያዎች ተመድበው በሽፍት እየሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አወቀ በዋናነት ለሊፍት ተጠቃሚዎች አስፈላጊውን መረጃ እና አገልግሎት መስጠት ማለትም ማስተናገድ፣ሊፍት መዝጋትናመክፈት እንዲሁም ችግሮች ሲኖሩ ከዋናው መስመር ጋር በመገናኘት እንዲስተካከል የማድረግ ስራዎች እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለተገልጋዮች ግንዛቤ መስጠትን በተመለከተ የአሳንሰር አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች ሊፍት እንዲጠቀሙ መረጃ ስለሚሰጡ አብዛኛው ተገልጋይ ሊፍት እንዲጠቀም በቀጣይ በመገናኛ ብዙኃን መልዕክት ይተላለፋል ሲሉ አክለዋል፡፡ አንዳንድ የባቡር አገልግሎት ተጠቃሚዎች አሳንሰር መስራቱ በተለይ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረ ገልፀው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ግን ግንዛቤ ሊኖረው ስለማይችል በተለያዩ መንገዶች ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡