የዜና መግለጫ

ኢ.ም.ባ.ኮ በ2ኛው አግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረም ተሳተፈ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: ኢ.ም.ባ.ኮ በ2ኛው አግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረም ተሳተፈ
የተጫነበት ቀን:  3/9/2018 3:13:52 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከየካቲት 26 ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች እንዲሁም የአለም አቀፍ ድርጅቶች ሃላፊዎች በሚሊኒየም አዳራሽ በተሳተፉበት 2ኛው አለም አቀፍ የአግሮ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በመሳተፍ የኮርፖሬሽኑን የስራ እንቅስቃሴ በአውደ ርዕይ አስጎበኘ፡፡ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያ በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎች ያላትን ምቹ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅማ፥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሚያስችላትን እድል ለመፍጠር እየሰራች ነው ሲሉ ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በበኩላቸው የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን እየሳቡ መሆኑን ገልጸዋል። የተለያዩ የሃገር ውስጥ አምራችና ማቀነባበሪያ ድርጅቶችም ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የወተት ተዋፅኦዎች፣ ማርና ቡና የመሳሰሉ የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶች ለእይታ ከቀረቡት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በፎረሙ የትራንስፖርት ዘርፍን የተመለከተ የፓናል ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር መስመር አክስዮን ማህበር አመራር አካላት በፓናል ውይይቱ ተሳተፈዋል፡፡ በፎረሙ ላይ ተሳታፊ የነበረው የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን የሚመለከት አበረታች ሃሳብና አስተያየቶች ከተለያዩ የፎረሙ ተሳታፊዎችና ጎብኝዎች የቀረበ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ ሃገሪቱ እያከናወነች ላለው ፈጣን እድገት ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የፕሮጀክቶች ዲዛይንና ተደራሽነት፣ የዜጎች የስራ እድል (በዋናነት ፕሮጀክቶች በሚካሄዱባቸውና ባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ላሉ አካላት) የመሳሰሉ በርካታ ጥያቄዎች ከጎብኝዎች የተነሱ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በተያያዘ የፎረሙ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባ- ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለቡ ባቡር ጣቢያን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱም በቻይና ባለሙያዎችና በኢ.ም.ባ.ኮ ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሚዲያ ግንኙነት ቡድን መሪ በሆኑት አቶ ዳግም ተረፈ ለጎብኝዎች አጠቃላይ ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉና አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል አቶ ማሩ ከበደ ከኢትዮጰያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አንዱ ናቸው፡፡ በከባድ የጭነት መኪኖች ረጅም ጊዜና እስከ ሰባት ቀን ሊቆይ የሚችለውን ጉዞ በሰዓታት ውስጥ መድረስ መቻሉ እኛ ከምንደግፈው የስራ ባህሪ ጋር ስናያይዘው ስጋና ወተት በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ ምርቶች ናቸው በመሆኑም በጭነት ላይ የሚፈጀውን ሰዓት መቀነስ መቻሉ ምርቶች ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን እንደጠበቁ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል በመሆኑ ባቡር ትራንስፖርት ለወጪ-ገቢ ንግዱ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልፀውልናል፡፡ ሌላኛው ሃሳባቸውን ያካፈሉን የጉብኝቱ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ፍስሃ ጌታቸው ሲሆኑ ዛሬ ካየሁት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ካከናወናቸው ትልቅ ስራ አንዱ የኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር መስመር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “እውነት ለመናገር ሃገሪቱ ከያዘቸው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስኬት አንዱ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ከአዲስ አበባ-ጅቡቲ ረዥም ጊዜ የሚፈጀውን የጭነትም ሆነ የህዝብ ትራንስፖርት ጊዜ ከማሳጠሩም በተጨማሪ ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ መፋጠን ትልቅ ድርሻ ይወጣል” ሲሉ አቶ ፍስሃ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ በሁለቱ ሃገራት መካከል ከሚኖረው ትስስርና የንግድ ስርዓቱን ከማቀላጠፉ በተጨማሪ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ቅሬታዎችን፣ በወደብ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚችል ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ የኢትዮያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያከናወነው ተግባር በሃገሪቱ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ደረጃ ትልቅ ደረጃ የሚያሰጠው መሆኑን በርካታ ጎብኚዎች በአድናቆት ገልፀዋል፡፡