የዜና መግለጫ

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በአለማቀፍ የሂሳብ አያያዝ ስታንዳርድ/ደረጃ/ የልምድ ልውውጥ አደረገ


ዜናውን የዘገበው:
ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
የዜናው ምስል: የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በአለማቀፍ የሂሳብ አያያዝ ስታንዳርድ/ደረጃ/ የልምድ ልውውጥ አደረገ
የተጫነበት ቀን:  1/26/2018 4:11:26 PM
የዜናው አካል:  የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በዓለማቀፍ የሂሳብ አያያዝ ስታንዳርድ ስርዓት ላይ ያደረገውን ጥናት ና ትግበራ በተመለከተ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ስር ካሉ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም በባቡር አካዳሚ ተገኝተው የልምድ ልውውጥ አደረጉ፡፡ በሀገሪቱ ያሉ የመንግስት ተቋማት በተለይ የልማት ድርጅቶች ከ2010 በጀት ዓመት ጀምሮ አለማቀፍ የሂሳብ አያያዝ ስታንዳርድ/ደረጃ/ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ተቋማቱ አሰራሩን አጥንተው ወደ ትግበራ ገብተዋል፡፡ አሰራሩን ተግባራዊ እያደረጉ ካሉ ተቋማት አንዱ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሲሆን በጥናት አሰራሩ ላይ የነበሩ ሂደቶችን በተመለከተ ከተለያዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ልምዱን አካፍሏል፡፡ በወቅቱም በኮርፖሬሽኑ ም/ ዋና ስራ አስፈፃሚ የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉአለም ጌታሁን ባደረጉት ንግግር ኮርፖሬሽኑ ወደዚህ ጥናት ለመግባት ሲጀምር በውስጥ ሀይል ለመስራት ወስኖ አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው ለስራው መሳለጥ የተለያዩ አጋዥ መፃህፍት በመግዛት መነሻ ማድረጋቸውንና በዘርፉ ልምድ ያላቸው ሁለት ባለሙያዎች በኮንትራት ቀጥሮ የጥናት ስራው በየሳምንቱ ከሙያው ጋር ተያያዥነት ካላቸው ኃላፊዎች ጋር በመሆን እየተገመገመ መሠራቱን ገልፀዋል፡፡ በኮርፖሬሽኑ አለማቀፍ የሂሳብ አያያዝ ስታንዳርድ/ደረጃ/ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወንድ ይፍራው ለገሰ በበኩላቸው የልምድ ልውውጥ መድረኩ ዓላማ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ስር ያሉ ተቋማት አለማቀፍ የሂሳብ አያያዝ ስርዓት እዲተገብሩ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ጥናት አድርገው ትግበራ መጀመራቸውን ጠቅሰው በዚህ መሠረት ኮርፖሬሽኑ የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገቡ ልምዱን እንዲያካፍል እድል በማግኘቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኮሚቴው ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት አጋዥ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ የድርጊት መርሀ ገብር ማውጣቱን አሳውቀው ኮርፖሬሽኑን የሚመለከቱ መስፈርቶች/Standard/ ቻርተር አካውንት በማዘጋጀት በተቋሙ እየተጠና ካለው የMIS ፕሮጀክት ጋር ተመጋጋቢ የሆነ የአሰራር መመሪያ /standard operating procedure/ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ወንድይፍራው ጠቅሰዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ የገቢ ምንጭ ብድር መሆኑ እና በጊዜ ሂደት የወለድና ምንዛሬ መጠኑ እየበዛ መሄድ ተጨማሪ ብድር ለመጠየቅ ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ጥናት በሚካሄድበት ወቅት ከኢትዮጵያ አካውንቲንግና ኦዲት ቦርድ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል አለመሰጠቱ፤የኮሚቴው አባላት በባቡር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልምድ አለመኖር እና በመደበኛ ስራና በተለያዩ ስልጠናዎች ምክንያት ለጥናቱ ሙሉ ጊዜያቸውን እንዳይሰጡ ማድረጉ የኮሚቴው አባላት ፈተናዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ ጥናቱ ሲጠና ከተቀመጡ አለማቀፍ መስፈርቶች ለኮርፖሬሽኑ ይሆናሉ ተብለው የተመረጡት 31 መስፈርቶች መሆናቸውንና ስራውን ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በየሳምንቱ እየተገመገመ መዘጋጀቱን አቶ ወንድ ይፍራው ገልፀዋል፡፡ የአሰራር ስርዓቱ የኮርፖሬሽኑን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት አድርጎ መሠራቱን ጠቅሰው አዳዲስ ሰራተኞች ሲመጡ ግንዛቤ ተሰጥቶ አንድ አይነት አሰራር እንዲኖር የሚረዳ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ጥናቱ በዋናነት የፕሮጀክቶች አፈፃፀምና አገልግሎት አሰጣጥን በተጨማሪም ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ማለትም በሰው ሀብት፣በፋይናንስ፣እና በህግ ስራ ክፍሎች የነበሩ ክፍተቶች ተለይተው እንዲካተቱ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በራሱ አቅም ጥናት አድርጎ ወደትግበራ መግባቱን አድንቀው በቀጣይ የቀሩ ሂደቶችን አሟልቶ ውጤታማ አፈፃፀም እንደሚያስመዘግብ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡