የወልዲያ/ሃራ ገበያ - መቀለ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት

216 ኪሜ የሚረዝመው ይህ የባቡር መስመር የአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎችን ያገናኛል፡፡ ፕሮጀክቱ እውን የሆነው እ.ኤ.አ ጥቅምት 15 ቀን 2014 ቢሆንም የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም በኢፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ በይፋ ተቀምጧል፡፡ የባቡር መስመሩ ባለ አንድ ነጠላ ሀዲድ እና 1.435 ሜ. ስታንዳርድ ጌጅ ስፋት ይኖረዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ነው፡፡

የግንባታ ስራው የሚያከናውነው ቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (CCCC) በተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሆን የማማከር እና የመቆጣጠር ሥራው /CIECC Jv with BES/ የተባሉ ሁለት የቻይና ኩባንያዎች ከአገር በቀል አማካር ኩባንያዎች ጋር በጋራ በመሆን ስራውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ የባቡር መስመሩ ከወልድያ/ሃራገበያ ተነስቶ በመስመሩ የሚገኙ የተለያዩ ከተሞችን በቅርብ ርቀት አቋርጦ ደረቅ ወደብ ያላት የመቐለ ከተማን መዳረሻ ያደርጋል፡፡ መስመሩ በ6 የግንባታ ቡድኖች እና ተጨማሪ በሶስት (የጥራት መቆጣጠርያ፤የድልድይ አካላት እና ርብራብ ማምረቻ፣የኤሌክትሪክ ምልክት ተግባቦት ስራዎች) በመከፋፈል የግንባታ ስራውን በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

የወልድያ/ሃራ ገበያ-መቀሌ የባቡር መስመር የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች

->  ወደ ጅቡቲ ወደብ በሚደረገው ጉዞ የሚወስደውን ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የወጭ-ገቢ ንግድን ያቀላጥፋል፡፡
-> የባቡር መስመሩ የሚያልፍበትን የአካባቢው ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡
-> በታዳሽ ኃይል(ኤሌክትሪክ) የሚንቀሳቀስ ባቡር ስለሚሆን የአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ የማስፈጸሚያ ማዕቀፍ ነው፡፡