የአዋሽ - ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት
እባክዎትን የፕሮጀክቱን ዋና ድህረ ገጽ ለመጎብኘት ይጫኑ!

392 ኪ.ሜትር የሚረዝመው የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት የቅድመ ዝግጅት ስራ ጥቅምት 08/2007 ዓ.ም ተጀምሮ ፤ የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም ላይ በኢፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ በይፋ ተቀምጧል፡፡ የባቡር መስመሩ ባለ አንድ ነጠላ ሀዲድ እና 1.435 ሜ. ስታንዳርድ ጌጅ ስፋት ይኖረዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራ ነው፡፡

በቱርኩ ያፒ መርከዚ ኮንትራክሽን ኢንዱስትሪ ኢንኮርፖሬሽን ተቋራጭነት፣በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አሰሪነት እና በተዋሀዱት የፈረንሳይ-ኢትዮጵያዊ ተቆጣጣሪ ድርጅት ሲስትራ-መልቲ ዲ ኮንሰልት አማካኝነት እየተገነባ ይገኛል፡፡ የአዋሽ-ኮምቦልቻ/ሃራገበያ የባቡር ፕሮጀክት በ1.7 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ እየተገነባ ነው፡፡ የባቡር መስመሩ ከአዋሽ ተነስቶ የኢንዱስትሪ መንደርና ደረቅ ወደብ ያላት ኮምቦልቻ ከተማን ማዕከል አድርጎ ወደፊት የባቡር መገናኛ የምትሆነውን ወልድያ/ሃራ ገበያን መዳረሻ ያደርጋል፡፡

ፕሮጀክቱ 10 የባቡር ጣቢያዎች የሚኖሩት ሲሆን ቁጥር 1፣ ቁጥር 3፣ቁጥር 7 እና ቁጥር 8 የሚገነቡት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የባቡሩን አጠቃላይ የኦፕሬሽን ስራና እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ እና የጥገና ማዕከል በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባ ይገኛል፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ 26 ባቡሮች የሚኖሩ ሲሆን 20ዎቹ የዕቃ መጫኛ 6ቶቹ ደግሞ የህዝብ ማመላለሻ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ የባቡር ትራንስፖርቱ አገልግሎት ሲጀምር ከአዋሽ ተነስቶ ወልድያ/ሃራ ገበያ ለመድረስ ከ4፡30-6፡30 ሰዓታት ይፈጃል፡፡

የአዋሽ - ኮምቦልቻ - ሃራ ገበያ የባቡር መስመር የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች

-> ወደ ጅቡቲ ወደብ በሚደረገው ጉዞ የሚወስደውን ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የወጭ-ገቢ ንግድን ያቀላጥፋል፡፡
-> የባቡር መስመሩ የሚያልፍበትን የአካባቢው ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡
-> በታዳሽ ኃይል(ኤሌክትሪክ) የሚንቀሳቀስ ባቡር ስለሆነ የአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ የማስፈጸሚያ ማዕቀፍ ነው፡፡
-> የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ከሌላው የአገሪቱ ክፍሎች ጋር በማስተሳሰር በህዝብ ለህዝብ ትስስር አንድ የሆነ የጋራ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመመስረት የሚደረገውን ጉዞ ያጠናክራል፡፡
-> ከምስራቅ ወደ ምህራብ የሚዘረጋው የትራንስ አፍሪካ የምድር ባቡር መረብ አካል ነው፡፡