የአዲስ - ጂቡቲ የባቡር አገልግሎት

የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ከሰበታ ተነስቶ ጅቡቲ ወደብ የሚዘልቅ ሲሆን 756 ኪሎ ሜትር ይረዝማል፡፡ የባቡር መስመሩ የሀገራችን ዋና ከተማ አዲስ አበባን ከጅቡቲና ዶራሌ የባህር በር ጋር ያገናኛል፡፡ የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባበር መስመር ግንባታ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መንግስታት በጋራ ምክክር የተሰራ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ/ሰበታ- መኤሶ-ደዋንሌ ድረስ ያለውን 656 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሲሰራ፤ ከኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር እስከ ጅቡቲ የባህር ወደብ ድረስ ያለው 100 ኪሎ ሜትር ደግሞ በጅቡቲ የባቡር ኮርፖሬሽን ተሰርቷል፡፡

የአዲስ አበባ/ሰበታ-ሜኢሶ-ደዋንሌ የባቡር ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ ተቋራጮች ለሁለት ተከፍሎ ተሰርቷል፡፡ የአዲስ አበባ/ሰበታ-ሜኢሶ መስመር በአንድ ምዕራፍ፤የሜኢሶ-ደዋንሌ መስመር ደግሞ በሌላ ምዕራፍ ተከናውኗል፡፡ የአዲስ አበባ/ሰበታ-ሜኢሶ የባቡር ፕሮጀክት እ.ኤ.አ የካቲት 12 ቀን 2012 ግንባታው ተጀመረ፡፡ የሜኢሶ-ደዋንሌ የባቡር ፕሮጀክት ደግሞ ከሁለት ወር በኋላ ሚያዚያ 12 ቀን 2012 ወደ ግንባታ ገባ፡፡ የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ የአዲስ አበባ/ሰበታ-ደዋንሌ የባቡር ፕሮጀክትን በአራት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ አጠናቋል፡፡ ከሰበታ እስከ ሜኢሶ የሚደርሰው የባቡር መስመር China Railway Group Limited (CREC) በተባለ የቻይና የስራ ተቋራጭ የተገነባ ሲሆን ከሜኢሶ እስከ ደዋንሌ የሚደርሰው የባቡር መስመር ደግሞ China Civil Engineering Consulting Corporation (CCECC) በተባለ የቻይና የስራ ተቋራጭ ተከናውኗል፡፡ በሁለቱም መስመር የግንባታውን ሂደት የተቆጣጠረው China International Engineering Consulting Corporation (CIECC) የተባለ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ የአዲስ አበባ/ሰበታ-ሜኢሶ-ደዋንሌ የባቡር መስመር ግንባታ ለማጠናቀቅ 3.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ኦፕሬሽን ገጽታ

የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ኦፕሬሽን የተሳፋሪና የጭነት የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ኦፕሬሽን ዋናው የስምሪት መቆጣጠሪያ የሚገኘው ለቡ የባቡር ጣቢያ ውስጥ ነው፡፡ በሁሉም የባቡር ጣቢያዎች የስምሪት መቆጣጠሪያ ዩኒቶች አሉ፡፡ ባቡሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት የተለያዩ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የኦፕሬሽን ስራውን የሚሰራ ልምድ ያለው አካል በአገር ውስጥ ባለመኖሩ በመንግስት አቅጣጫ ተሰጥቶ ከስድስት- ሰባት ዓመታት ዓለም አቀፍ ኩባንያ ስራውን ይይዝና እግረ መንገድ በዚህ ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያና የጅቡቲ ባለሙያዎች ተምረው ይቀበላሉ የሚል አቅጣጫ ተሰጥቶ ጨረታው ወጥቶ አሸናፊው ታውቆ ውል ተፈርሟል፡፡

የባቡር ኦፕሬሽኑን የሚያስተዳድር የማኔጅመንት ኮንትራክተር ለቻይና ኩባንያዎች ጥምረት (CREC & CCECC) የተሰጠ ሲሆን በማኔጅመንት ኮንትራቱ የኦፕሬሽንና የጥገና ስራ ይሰራል፡፡ ማኔጅመንት ኮንትራክተሩን የሚያስተዳድር የሁለቱ ሀገራት ሼር ያለበት የአዲስ አበባ - ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የምድር ባቡር ሼር ካምፓኒ ተቋቁሟል፡፡ በመቀጠል የሁለቱን ሀገራት የሚያስተሳስር የሁለትዮሽ ስምምነት /Bilateral Agreement/ ተፈርሞ ለፓርላማ ተልኮ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡ ሌላው የባቡር አገልግሎቱን ስራ ለማስጀመር ወሳኝ የሰው ሃይል ዝግጅት፣ የሀይል አቅርቦት፣ የመሰረተ-ልማት (የአገናኝ መንገዶችና ሃዲዶች ግንባታና ዝረጋታ፣ የማከማቻ አገልግሎቶች /Containers/ እና የደረቅ ወደቦች) ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የምድር ባቡር አግልግሎት በእቅዱ መሰረት ከሆነ እ.ኤ.አ ጥቅምት 29 ቀን 2017 የሙከራ ስራው ተጠናቆ ርክክብ ከተደረገ በኋላ ሼር ካምፓኒው ከማኔጅመንት ኮንትራክተሩ ጋር ሆኖ ስራ ይጀምራል፡፡